የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወነ መሆናቸው ተገለጸ

ነሐሴ 17/2015 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያን የቀጣናው ሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ከህዝብ ብዛት ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የፈጣንና ግዙፍ ኢኮኖሚ ቢኖራትም የወጪና ገቢ ንግዷ በዋናነት በጅቡቲ ወደብ በኩል እንደሚከናወንና ይህም እያደገ ከመጣው የተቀላጠፈ የሎጅስቲክ አግልግሎት ፍላጎት አንጻር ትልቅ ማነቆ መፍጠሩ ነው የተገለጸው፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚሸከም የተቀላጠፈ የወጪና ገቢ ንግድ ሎጂስቲክስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

እስካሁን 96 በመቶ የሚሆነው የወጪና ገቢ ንግድ በጅቡቲ በኩል እንደሚደረግ ገልጸው ይህም ከሚፈጠረው መጨናነቅ ባሻገር ከጊዜና ወጪ ረገድ ትልቅ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም የሚያስችሉ ስራዎች እየከናወነች መሆኑን ተናግረው በዚህም የበርበራ ኮሪደር እና የኬኒያውን ላሙ ወደብን ጨምሮ አማራጭ ወደቦችን በማየት ከሚመለከታቸው ሀገራት ጋር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በመልማት ላይ የሚገኘውን የላሙ ወደብ ለመጠቀም ከኬኒያ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ሁለቱን ተጨማሪ ወደቦች መጠቀሟ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት የሚያስተሳስረው ‘ላፕሴት’ ለተሰኘው ፕሮጀክት መሳለጥ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አመላከተዋል።

የላሙ ኮሪደር ወደ ስራ መግባትም የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድን በማሳለጥ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ እና እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ ለማስተናገድ የሎጂስቲክ ሥርዓት ማዘመን እና ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።

የብዝኃ ወደብ አጠቃቀም ለማስፋትም ቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የላፕሴት ፕሮጀክት በአማራጭ የወደብ አጠቃቀም ከማሳለጥ በተጨማሪ አፍሪካን እርስ በርስ በንግድ ለማስተሳሰር ግብ ይዞ ወደ ትግበራ ለገባው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስኬት ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያን ጨምሮ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማትን በመዘርጋት ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ማዕከል እንድሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጎረቤት ሀገራት በኩል የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች ሲጠናቀቁ በጋራ የመበልፀግ፣ አፍሪካን የማስተሳሰር እንዲሁም ለኢትዮጵያም ትልቅ የገበያ ዕድል ለመፍጠር ሁነኛ ፋይዳ እንዳለው ነው ያነሱት።

የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ በላብሴት ሰባት ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ ገልጸው ኢትዮጵያ እስከ ሞያሌ ያለውን ፈጣን መንገድ ጨምሮ የበኩሏን ኃላፊነት መፈጸሟን ተናግረዋል።