የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቋቋም ምሁራን ፊት መሪ ሆነው መቆም እንዳለባቸው ተገለጸ

መስከረም 29/2014 (ዋልታ) የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቋቋም ምሁራን ፊት መሪ ሆነው ለኢትዮጵያ መቆም እንዳለባቸው ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ዋቅጋሪ ነጋሪ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት የውጭ ጣልቃ- ገብነትን ለመቋቋም ምሁራን ፊት መሪ ሆነው ለኢትዮጵያ መቆም አለባቸው።

ምሁራን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በያገባኛል ስሜት ኃያላን ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያሳዩትን ጣልቃ ገብነት ጥበብን በተላበሰ መልኩ ሊመክቱ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ምሁራን ዕውቀታቸውን ከማካፈል ጎን ለጎን ሀገር እንደ አሁኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በምትገባበት ወቅት ልምድና እውቀታቸውን ተጠቅመው የዓለም አቀፉን ጫና የማምከን ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።

እንደ ዶክተር ዋቅጋሪ ገለፃ፤ በኢኮኖሚ በለፀግን የሚሉ ሀገራት እጃቸው ረጅም ነው፤ ስለዚህም በረጃጅም እጆቻቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሄዱበት ያለውን መንገድ ማጋለጥና የዓለም ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጠረ ያለውን ጫና በአግባቡ እንዲገነዘበው የማድረግ ሥራ ከምሁራን ይጠበቃል።