የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ከአፍሪካ ሕብረት ጎን በመቆም የሰላም ጥረቱን የተሳካ ለማድረግ እንዲደግፍ ጥሪ ቀረበ

ነሐሴ 11/2014 (ዋልታ) የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ከአፍሪካ ሕብረት ጎን በመቆም ኢትዮጵያ በሰሜኑ የምታደርገው የሰላም ጥረት የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኮሚቴው የሰላም ምክረ ሃሳቡን በተመለከተ ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የሰጠውን ማብራሪያ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ መግለጫ

መንግስት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት የጀመረውን ጥረት ከዳር ለማድረስ የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ፣ እስካሁን የነበረውን እንቅስቃሴ፣ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

እንደሚታወሰው ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለሰላም እድል ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ለአብነትም የተናጠል የሰብዓዊነት ተኩስ አቁም ማወጅን ጨምሮ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳት፣ እስረኞችን መፍታት፣ የሰብዓዊ ድጋፍን በከፍተኛ ሁኔታ የማሳለጥ እና መሰል እርምጃዎችን ወስዷል።

ከእነዚህ እርምጃዎች በተጨማሪ፣ መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እና ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ይታወቃል ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የሰላም ንግግር ያለቅድመ ሁኔታ በየተኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመጀመር ያለውን ዝግጁነት መግለፁ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት የሰላም አማራጭን በዘላቂነት እውን ለማድረግ እና በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል፣ በተለይም የግጭት ሰለባ እና ተጋላጭ በሆኑ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ዜጎች በእለት ተእለት ኑሮዋችው እየገጠማቸው ያለውን ችግር መቀረፍ እንደሚገባ፤ በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማድረስ ይቻል ዘንድ፣ እንዲሁም የመሰረተ ልማት እና የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ስራ ለማስጀመር አስቻይ የሆነ ሁኔታ በፍጠነት ለመፍጠር፤ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአጭር ጊዜ ላይ መድረስ እንደሚገባ ኮሚቴው አጽኖት ሰጥቶ ተወያይቷል።

ይህን ሂደት ለማፋጠን ይረዳ ዘንድ፣ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሰረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሃሳብ ላይ ውይይት በማድረግ የምክረ ሃሳብ ሰነዱን በማዳበር አጽድቆዋል። እንዲሁም ኮሚቴው ይህ ምክረ ሃሳብ በተቻለ ፍጥነት ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ ወስኗል። እንዲሁም  የአፍሪካ ህብረትን የሰላም ጥረት በሚደግፉ አካላት ትብብር በመታገዝ በአጭር ጊዜ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ፣ የሰላም ምክረ ሃሳቡን በተመለከተ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ  ማብራሪያ እንዲሰጥ በወሰነው መሰረት ይህ ተግባር በዛሬው እለት ተከናውኗል።

በተጨማሪም ኮሚቴው፣

▪️ ወደተኩስ አቁም ስምምነት ሲገባ በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ ፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ፣ አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን፤

▪️ የአፍሪካ ህብረትም የሰላም ንግግሩ በአስቸኳይ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ዘንድ፣ የሰላም ንግግሩ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጠነት ወሰኖ ንግግሩ እንዲጀመር፣ ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ገምግሟል።

እንዲሁም የሰላም አብይ ኮሚቴው፣ ከላይ የተመላከቱትን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ፣ የሚመለከታቸው ንዑስ ኮሚቴዎች እና ተቋማት አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ከወዲሁ እንዲያደርጉ አሳስቧል። በተጨማሪም ለሰላም አማራጩ እውን መሆን  የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየውን ድጋፍ በማድነቅ፣ ይህ ድጋፍ ተጥናክሮ እንዲቀጥል፤ የአለም አቀፉ ማህበረሰብም ከአፍሪካ ህብረት ጎን በመቆም የሰላም ጥረቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋትፅዖ እንዲያበረክት ኮሚቴው ጥሪ አስተላልፏል።