የዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ ኢትዮጵያን ካለማወቅ የመነጨ ነው – የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ኅዳር 25/2014 (ዋልታ) የትምህርት ሚኒስቴር የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ለመሰብሰብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርታቸው ለሁለት ሳምንት እንዲያቆርጡ ማዘዙን ዓለም ዐቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በተሳሳተ መልኩ እየዘገበ መሆኑን መንግስት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ መንግስት ለጦርነቱ ማዋያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ወስኗል ሲል ቢቢሲ መዘገቡን አስታውሰው ይህም ስለ ኢትዮጵያዊነት ካለማወቅ የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተማሪዎች የበጎ ፈቃድ አግልግሎት ስራ መሰራት የተጀመረው አሁን አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ ተማሪዎች ማኅበሰባቸውን ማገልገል የቆዬ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የዓለም ዐቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ መረጃዎችን በማሰራጨት ዓለምን ማደናገራቸው ቀጥሏል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብኣዊ ድጋፍ ለማዳረስ እያደረገ ያለውን ጥረት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው እያለፉት መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍን በመኪና እና በአውሮፕላን ወደ ትግራይ ክልል ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልል አሰቃቂ ጥቃት ሲፈጽም ሽፋን ያልሰጡት የዐለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳቸው ሌላ ስለሆነ ነው በማለት ለሕዝብ የተሳሳተ የመረጃ ዘመቻ ለመመከት የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳሳበዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ