የዓባይ ጉዳይ በትምህርት ስርዓት ተካቶ ሊቀርብ ይገባል-  የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር 

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የዓባይ ጉዳይ በኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ ቢቀርብ ግንዛቤ ለተተኪው ትውልዱ ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስገነዘበ፡፡

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ቀደም ባሉት ዘመናት እነ ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ አቤ ጉበኛ፣ አያልነህ ሙላቱ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ ኃይሉ ገብረ ዮሃንስ (ገሞራው)፣ ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ ኮሎኔል ሞገስ ሀብቱ እና የመሳሰሉት የመድረክ ሰዎች፣ ገጣሚያን እና ባለቅኔዎች በዓባይ ላይ ብዙ ቢሉም ፀፀትንና የተለያዩ ስሜቶችን ከማንፀባረቅ ባለፈ ትውልድ ለመቅረፅ የነበራቸው ፋይዳ እምብዛም እንደነበረ ያወሳል፡፡

አሁን ላይ ግን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር የዓባይ ዘመን ብዕሮች ከሃዘን፣ ከቁጭትና ከእንጉርጉሮ ተላቀው በተስፋ፣ በጥቅም፣ በሕብረት እና በአንድነት ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ ለተተኪው ትውልድ ተስፋን የሚያሰንቁ የጥበብ ስራዎች መተካታቸውን ማህበሩ ያነሳል፡፡

በቀጣይም በዓባይ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ የጥበብ ስራዎች ፋይዳ እንዲኖራቸው በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካተው ሊቀርቡ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ይህም በዓባይ ጉዳይ ላይ ለማስረዳት የሚችል በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚረዳ መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ከግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጋር በመተባበር አንጋፋና ወጣት ደራሲያን የተሳተፉበት ሁለት የጽሁፍ ስራዎች መታተማቸውን ጠቅሷል፡፡