አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተመርቆ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ ከ246 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ግሩም ግርማ÷ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለህዝብ ክፍት ከተደረገ ጀምሮ በየእለቱ በርካታ ጎብኚዎችን እያስተናገደ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን ድል የሚዘክር መታሰቢያ በመገንባቱ መጪው ትውልድ የአባቶቹን ጀግነት እንዲወርስ የሚያደርግ መሆኑን ተናግርዋል።
ከመጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ባሉት ወራት ከ246 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለጎብኚዎች ክፍት ከተደረገ ጀምሮ ከጎብኚዎች፣ ከተለያዩ ሁነቶች እና ከሌሎች አገልግሎቶች 123 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ እንደተገኘ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡