ግንቦት 28/2014 (ዋልታ) የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለሁለተኛ ጊዜ ያሰባሰባቸውን ከ2 ሺሕ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍ አበረከተ።
የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ ሳሙኤል ወልደጊዮርጊስ መጻሕፍቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአብሮሆት ቤተ መጽሐፍት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ለሆኑት ታምራት ሀይሉ (ዶ/ር) አስረክበዋል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ከ13 ሺሕ 400 በላይ መጻሕፍት ማበርከቱን አስታውሰው በጠቅላላው በሁለት ዙር የተበረከተው መጻሕፍት ቁጥር ከ15 ሺሕ 700 በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
መጻሕፍቱ የታሪክ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት፣ የምርምርና የትምህርት አጋዥ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክና እሴት የሚያጎሉ መጻሕፍት በትኩረት መሰብሰባቸውንም ነው የተናገሩት።
ድርጅቱ መጻሕፍቱን ያሰባሰበው ከተቋሙ ሰራተኞች፣ ከተባባሪ አካላት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከግለሰቦች መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍ “ሚሊዮን መጽሐፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ኃሳብ መጻሕፍትን ለማሰባሰብ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡