የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በድጋሚ ሊመረጡ ነው


ሰኔ 7/2016 (አዲስ ዋልታ) የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፓርቲ መሪ እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራሞፎሳ ለሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመን ፕሬዝዳንት ሆነው ሊመረጡ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ዳግም የሚመረጡት ገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ እና ተፎካካሪው የዴሞክራቲክ አሊያንስ (ዲኤ) ፓርቲ የጥምር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ይህ የሆነው በባለፈው ወር ምርጫ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ አብላጫውን ድምፅ በማጣቱ ሲሆን በምርጫው ፓርቲው አርባ በመቶ ድምጽ አግኝቷል።

ተፎካካሪው የዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ 22 በመቶ ድምፅ በማግኘት ተከትሏል፡፡

በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የሚመሰረተው ጥምር መንግስት ሲሪል ራማፎሳ ዳግም ፕሬዝደንት ሆነው እንዲመረጡ እድል ይሰጣቸዋል ተብሏል።

የኤኤንሲ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ እንደገለጹት ጥምረቱ ብሄራዊ አንድነት ለመፍጠር ትልቅ እርምጃ ነው፡፡

አዲሱ ፓርላማ መቀመጫውን መያዙን ተከትሎ አፈጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ ከመረጠ በኋላ የፕሬዝዳንት ምርጫ ያከናውናል፡፡

የዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ መሪ ጆን ሰቴሁንሰን ጥምረቱ በደቡብ አፍሪካ አዲስ ታሪካዊ ምእራፍ መሆኑን ገልጸው ምርጫው የደቡብ አፍሪካ ህዝብ አንድ ፓርቲ ብቻ እንዲያስተዳድረው እንደማይፈልግ ያሳየበት ነው ማታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የኤኤንሲ ፓርቲ ለመጀመርያ ጊዜ በፈረንጆቹ 1994 በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣን ከያዘ በኋላ አብላጫውን ድምጽ ሲያጣ ይህ የመጀመርያው ነው፡፡