የደቡብ ክልል ም/ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

መጋቢት 9/2014 (ዋልታ) የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ጉባኤውን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ለብሔራዊ መግባባት አደናቃፊ የሆኑ በርካታ ተንከባላይ አገራዊ ውስብስብ ችግሮችን ሁሉን አካታች በሆነ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ፣ የዜጎች ወንድማማችነትን የሚያጎለብትና የጋራ አገራዊ ራዕይ የሚሰንቅ፣ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችንና ግጭትን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቅ ውጤታማ ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ ሕዝቡ የበኩሉን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በየጊዜው እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም ካለው ውስብስብ ችግር አንፃር ገና መቀረፍ ያለባቸው ቀሪ የቤት ሥራዎች ይኖሩናል ያሉት አፈ ጉባኤዋ ለዚህም መንግሥት፣ አምራች፣ አከፋፋይ ነጋዴዎችና ሸማቹ ኅብረተሰብ ተቀናጅቶ መስራትን ይጠይቃል ማለታቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡