የደቡብ ክልል ነዋሪዎች በትግራይ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ከ11.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

የደቡብ ክልል ነዋሪዎች በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል ከ11.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አበረከቱ።

የክልሉ ተወካዮች ከነዋሪዎች የተሰበሰበውን ድጋፍ ዛሬ በመቀሌ ተገኝተው ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስረክበዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰማን ሽፋ ከነዋሪዎች የተላከውን 3 ሺህ 200 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና የቅንጬ እህል ማድረሳቸውን ገልፀዋል።

“መደጋገፍ የኢትዮጵያዊነት እሴት ነው” ያሉት አቶ ሰማን፤ ከትግራይ ሕዝብ ጎን በመቆማቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ የደቡብ ክልል ነዋሪዎች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ የሕዝቦች መተሳሰብ ከወሰን በላይ መሆኑን ያየንበነት ነው ሲሉ ገልፀዋል።

“አብሮነት የሠላም ተምሳሌት ነው” ያሉት ዶክተር ሙሉ፤ ድጋፉ የህዝቦች አንድነት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ በሚሻበት ጊዜ የደቡብ ክልል ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች ክልሎችም ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል ለትግራይ ክልል ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።