የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር ለህልውና ዘመቻ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቀለ

አለበል ዘለቀ

ጥቅምት 01/2014 (ዋልታ) የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነው አለበል ዘለቀ ለህልውና ዘመቻ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ወደ ማሰልጠኛ ማዕከለ መግባቱ ተገለፀ።

የማስተርስ ድግሪ ተመራቂና የሁለት ልጆች አባት የሆነው አለበል የወሰነው ውሳኔ ከወራሪው ትሕነግ ጋር እየተደረገ ላለው የህልውና ዘመቻም አርዓያ የሚሆን ተግባር መሆኑን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ለዋልታ ቴሌቪዥን ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የውሀ ምህንድስና መምህር የሆነው አለበል በህልውና ዘመቻው ቀደም ባሉት ወራት ህብረተሰቡን በማንቃት በማስተባበርና እንደማንኛውም ዜጋም ለመከላከያ ከደመወዙ መዋጮ ሲያደረግ ቆይቷል፡፡

በዚህ ተሳትፎ ብቻም ሳይወሰን ሀገርና ህዝብን ከወራሪው ትሕነግ ጥፋት ለመታደግ የመከላከያን ጥሪ ተከትሎም ምዝገባ በማድረግ መስፈርቱን አልፎ መስከረም ላይ  ወታደራዊ ማሰልጠኛን መቀላቀሉ ተገልጿል። ውሳኔውም የአካባቢውን ማህበረሰብ ያስደነቀ፤ ባለቤቱና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አባላትን ያኮራ ሆኗል ነው የተባለው።

ውሳኔው በከፍተኛ የስራ መድብ ላይ ላለና ቤተሰብ ላለው አንድ ግለሰብ የማይታሰብ ቢሆንም አለበል ግን ለሀገሩ የህይወት መስዋእትነት ጭምር  ለመክፈል ቁርጠኛ መሆኑን መከላከያን በመቀላቀል አሳይቷል።

አለበል ዘለቀ በዚህ ግዳጅ ላይ ሲሰማራ ለባለቤቱና ሁለት ልጆቹ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ከደጀን ህዝብ የሚጠበቅ ነውና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲት አለሁላችሁ ብሏቸዋል። ዩኒቨርሲቲው የአለበልን ሙሉ ደመወዝ ከመስጠት በተጨማሪ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት በነፃ ለዘማቹ አለበል ባለቤት እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የዘማች አለበል  ባለቤትና ልጆች ብቸኝነትና ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው የአካባቢው ማህረሰብ ከጎናቸው እንደሚሆንም ነው የተገለፀው፡፡ ወጣቱ አለበል ኢትዮጵያ የህልውና ፈተና ውስጥ በወደቀጭበት ወቅት የሀገር መከላከያን ለመቀላቀል መወሰኑ ለሌሎችም አርዓያ የሆነ ተግባር መሆኑን የስራ ባልደረቦቹ አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ሙያ ለህልውና ዘመቻው የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አስተያየታቸውን ለዋል የሰጡት ባልደረቦቹ ገልፀዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እንደተቋም ለህልውና ዘመቻው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ እንደ አለበል አይነቱም የተቋሙ ባለሙያ ሀገሪቱን ከገባችበት የህልውና ፈተና ለመታደግ  የውትድርናው አለም ተቀላቅሏል፡፡

በደምሰው በነበሩ