የዳያስፖራውን ጉብኝት የሚያስተባብር የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ መግባት

የዳያስፖራውን ጉብኝት የሚያስተባብር የልዑካን ቡድን

ጳጉሜ 03/2013 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የሚያካሂዱት ጉብኝት የሚያስተባብር የልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ገባ።

የልዑካን ቡድኑ ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የቱሪዝም ኢትዮጵያ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት ባዘጋጀው “እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ” በሚል መሪ ሀሳብ መርኃግብር ከጳጉሜ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ ነው።

ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት መርኃግብሩን የሚያስተባብሩት ስድስት የምክር ቤቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሲሆን፣ ከሰሜን አሜሪካ፣ እስያ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ የሚመጡ 500 ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ነው ተብሏል።

በመርኃግብሩ ዳያስፖራው “ዓባይን እንጎብኘው” በሚል መሪ ሀሳብ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ እንደሚጎበኝና የግድቡን ሰራተኞች እንደሚያበረታቱም ይጠበቃል።

የሸገር ማስዋብና በገበታ ለአገር ፕሮጀክት የተካተተው ጎርጎራ የጉብኝቱ አካል እንደሚሆንም የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።