የዳጉሩ-ጋላሞ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) በኢትዮ-ጅቡቲ የጋላፊ ኮሪደር አካል የሆነው የዳጉሩ-ጋላሞ የአስፋልት መንገድ የግንባታ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተከሄደ፡፡

በኢትዮ-ጅቡቲ የጋላፊ ኮሪደር አካል የሆነው የዳጉሩ-ጋላሞ 30 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በጅቡቲና ሳዑዲ አረቢያ መንግሥታት መካከል በተደረሰው የትብብር ሥምምነት መሰረት የሳዑዲ የልማት ፈንድ ለመንገድ ግንባታው በሰጠው የፋይናንስ ድጋፍ ነው የግንባታ ሥራው የተጀመረው።

በስነ-ሥርዓቱ ላይ የጅቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱለቃዲር ካሚል ሀመድ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሀሰን ሁሙድ ኢብራሂም፣ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ በጅቡቲ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር እንዲሁም ሌሎች የአገራቱ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የመንገድ ግንባታው የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር አካል መሆኑና የሁለቱን አገራት ትሥሥር ከማጠናከርና የኢትዮጵያን የወጪ-ገቢ ምርቶች ከማሳለጥ አኳያ የሚኖረው አስተዋፀኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተነስቷል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከጅቡቲ ወደቦች ወደ ኢትዮጵያ የሚጓጓዙ ምርቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለማጓጓዝ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በመኪኖች ላይ ይደርስ የነበረ ጉዳትን እና የጊዜ መጓተትን እንደሚቀንስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል፡፡