የዴሞክራሲ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር መንግሥታዊ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉ ተገለጸ

ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) የዴሞክራሲ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር የሕግ ማሻሻያዎችና መንግሥታዊ ድጋፎች እንዲጠናከሩ እንሰራለን ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የዴሞክራሲ ተቋማት ያከናወኗቸውን የማሻሻያ የለውጥ ሥራዎች የተመለከተ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ተቋማት ያከናወኗቸው የማሻሻያ ሥራዎችና ያጋጠሟቸው ችግሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻል፣ ወቅቱን ያማከሉ የቴክኖሎጂ ለውጦችና የሰው ኃይል ክህሎትን የማሳደግና አቅም የማደራጀት ተግባራት መከናወናቸውን ተቋማቱ አብራርተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የዴሞክራሲ ተቋማትን “የምክር ቤቱ ክንዶች” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

የተቋማት መጠናከር በአንድ አገር ውስጥ ሥርዓት እንዲኖርና አገርም እንዲገነባ ዋነኛ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የተቋማቱን አቅም የሚያጎለብቱ የሕግ ማሻሻያዎችና መንግሥታዊ ድጋፎች እንዲጠናከሩ እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በተቋማት ግንባታ ሂደት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት ፅኑ መሰረት ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው በሚዲያ ተቋማት “የተለያዩ ድምፆችን የማሰማትና የፍትሐዊነት ችግሮች ስለሚስተዋሉ ሊስተካከሉ ይገባል” ብለዋል።

የዴሞክራሲ ተቋማቱ ሪፖርት በማውጣት ብቻ ገለልተኝነታቸውን ከማሳወቅ አልፈው ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የቁጥጥር ሥራ እንዲከናወን መስራት አለባቸው ብለዋል።

በመድረኩ የተቋማት ኃላፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተው መልካም ተሞክሮዎችን በማስቀጠል ችግሮችን መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።