የድንጋይ ከሰል የማዕድን ግብአቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሂደት በቅርቡ ይጠናቀቃል – የማዕድን ሚኒስትር

                                                                 የማዕድን ሚኒስትር  ታከለ ኡማ

ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) የውጪ የድንጋይ ከሰል የማዕድን ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የሚተካበት ሂደት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ አስታወቁ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ የተመረተ የድንጋይ ከሰል ምርት መጠቀም መጀመራቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሲሚንቶ ምርቱ እየጨመረ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

አሁን እያየን ያለነው የምርት ጭማሪ ጅማሬውን ነው ያሉት ሚኒስትሩ በቅርብ ጊዜ የድንጋይ ከሰልን የሚያመርቱ ተቋማት የግንባታ ስራቸውን አጠናቀው ወደ ስራ እንደሚገቡና የሚኖረው የሲሚንቶ ምርት ፍላጎቱን የሚመጥን እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ዛሬ በደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጉብኝት ያደረጉት ኢንጂነር ታከለ የፋብሪካው ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ መመልከታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

የውጪ የድንጋይ ከሰል የማዕድን ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የምንተካበት ሂደትም በቅርቡ እናጠናቅቃለን ብለዋል።