የዶሮ በሽታ በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ኅብረተሰቡ ያለምንም ስጋት ዶሮና እንቁላል መመገብ ይችላል – ግብርና ሚኒስቴር

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) በቅርቡ የተከሰተው የዶሮ በሽታ በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ኅብረተሰቡ ያለምንም ስጋት ዶሮና እንቁላል መመገብ እንደሚችል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ጉዳዩን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ባሳለፍነው ሰኔ ወር መባቻ በቢሾፍቱና በምዕራብ አዲስ አበባ የተከሰተው የዶሮ በሽታ ወረርሽኝ በዶሮ እርባታ ቦታዎች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

በሽታው እንደተከሰተ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል ተሰማርቶ የበሽታውን ሥርጭት የመግታት አፋጣኝ ምላሽ መውሰዱን ገልጸዋል።

በወቅቱ ለዶሮ እርባታ አገልግሎት ከውጭ የሚገባው የለማ እንቁላልና ዶሮና የዶሮ ውጤቶች ዝውውር ባለበት እንዲገታ የጥንቃቄ መመሪያዎች ለሚመለከታቸው አካላት መተላለፉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ዶሮና እንቁላል አመጋገብ ላይ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ መተላለፉን ገልጸው በሂደትም የጥንቃቄ መመሪያዎች እየተሻሻሉ መሄዳቸውን ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ምክንያት በሽታውን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉንም በመግለጫው ገልጸዋል።

አሁን ላይ ምንም አይነት የበሽታ ስጋት ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ዶሮና እንቁላል ያለስጋት በማብሰል እንዲጠቀም፤ ዶሮ አርቢዎችም በሙሉ አቅማቸው ዶሮ በማርባት ለገበያ እንዲያቀርቡ መወሰኑን ተናግረዋል።

ሆኖም በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ዜጎች በማንኛውም ጊዜ የሚያደርጉትን ‘ባዮ-ሴኪዩሪቲ’ የተሰኘውን የዶሮ እርባታ ጥንቃቄ ሥርዓትን ባጠናከረ አግባብ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ በሰው ጤና ላይ ጉዳት ያስከተለው ጉዳት ካለ ለመለየት ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ጥናት ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በጥናቱ ውጤት መሰረትም እስካሁን በሽታው በአንድም ሰው ላይ የጤና ችግር አለማድረሱ መረጋገጡን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በወረርሽኙ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎች መሞታቸውን ጠቅሰው፤ በዶሮና የዶሮ ውጤቶች እንቅስቃሴ ላይ እገዳ መጣሉ ደግሞ ዘርፉ ላይ ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል፡፡

እንደ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ገለጻ፤ ወረርሽኙን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት የዶሮ እርባታ ሥርዓትን ማሻሻልና የአርቢዎችን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሰጥቷል፡፡

በተለይ በዶሮ እርባታ የሚሳተፉ ዜጎች ዘወትር ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መተግበር እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡