የጀኔራል ዋቆ ጉቱ ፋውንዴሽን ማስጀመሪያ መርኃግብር ተካሄደ

የጀኔራል ዋቆ ጉቱ ፋውንዴሽን

ሚያዝያ 12/2013 ዋልታ) – የጀኔራል ዋቆ ጉቱ ፋውንዴሽን ማስጀመሪያ መርኃግብር በባሌ ሮቤ ከተማ ተካሄደ፡፡

የባሌ ሮቤ ከተማ አስተዳደር ለጀኔራል ዋቆ ጉቱ ፋውንዴሽን 21.8 ሚሊየን ብር የመደበ ሲሆን፣ በከተማው አደባባይ ላይ የመታሰቢያ ሐውልታቸው ግንባታም በይፋ ተጀምሯል።

ፋውንዴሽኑን በይፋ ያስጀመሩት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ እንዳሉት፣ የባሌ ጀግኖች ከዛሬ 70 እና 80 አመታት በፊት ሲታገሉለት የነበረው በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ድንቁርና እንዲጠፋ እና ሀገሪቱ የተሻለች እንድትሆን ነበር።

የዛሬው ትውልድ ትግሉን ወደ ውጤት ቀይሮ በተግባር እየሰራ ስለመሆኑ አሁን ላይ በባሌ ሮቤ ከተማ የምናያቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

የባሌ ሮቤ ከተማ ከንቲባ ገዛኸኝ ደጀኔ በበኩላቸው፣ ጀኔራል ዋቆ ጉቱ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ ጭቆና እንዲቆም፣ ሁለንተናዊ እድገት እንዲመጣ ብርቱ ትግል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ጀኔራል ዋቆ “ባሪያነትን ከስሩ እንነቅላለን ባንችል እንኳን ልጆቻችንን እናሳድግበታለን” እንዳሉት ሁሉ የአሁኑ ትውልድም በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየሰራ የእርሳቸውን የመታሰቢያ ሐውልት ይገነባል ሲሉ ተናግረዋል።

ጀኔራል ዋቆ ጉቱ የባሌ ምድር ካፈራቻቸውና ለኢትዮጵያ እድገት ብርቱ ትግል ካደረጉ ጀግኖች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

(በደረሰ አማረ)