የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ትግበራ ላይ ውይይት ተካሄደ

ጥቅምት 25/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት የተቀናጀ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ማዕቀፍ ሀገራዊ የድርጅት መርሃግብር ትግበራ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡

የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ቱሉ በሻ (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ ለማህበራዊ፣ አካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያለው ከመሆኑም በላይ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ አዝማሚያ ያላቸው ተግዳሮቶችን ለመቋቋም፣ ተጽኖአቸውን ለመቀነስ እንዲሁም ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡

ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ምን የት ቦታ፣ መቼ፣ በምን መጠን፣ ለምን እና እንዴት ተፈጠረ የሚለውን ወሳኝ መረጃ ለውሳኔ ሰጪ፣ ለፖሊሲ አውጪ እና ለተጠቃሚ አካላት መስጠት የሚያስችል ወሳኝ ዲጂታል ገንዘብ ወይንም ወሳኝ መሠረተ ልማት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዓለም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፈጣን እድገት እያሳዩ በመምጣታቸው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በእጅጉ እንዲሻሻል እና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡

ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን የሚያመርቱ ተቋማት ዳታን ከማምረት ባልተናነሰ አግባብ የመረጃ ወቅታዊነት እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከመቼውም በላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡