የጃዊ ወረዳ ፋኖ አባላት የክተት ጥሪውን በመቀበል ወደ ግንባር ዘመቱ

የጃዊ ወረዳ ፋኖ አባላት

ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) የጃዊ ወረዳ ፋኖ አባላት የአማራ ክልል መንግስት ያቀረበውን የክተት ጥሪ በመቀበል ወደ ግንባር እየዘመቱ ነው።

ዘራፊውንና አሸባሪውን ሕወሓት ለመደምሰስ ወደ ግንባር ለሚዘምቱ የጃዊ ወረዳ ፋኖ አባለት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።

በሽኝት ፕሮግራሙ የፋኖ አባላት በመንግስት አደረጃጀት በመካተት የጠላትን ኃይል ለመደምሰስና ለመፋለም መወሰናቸው ተገልጿል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ እንግዳ ደኛው የአማራ ክልል መንግስት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል በዞኑ የታጠቁ የሚሊሻ አባለት ወደ ግንባር እየዘመቱ መሆናቸውን አንስተዋል።

አሸባሪውን ሙሉ በሙሉ ደምስሰውና ከኢትዮጵያ ምድረ ገፅ አጥፍተው በትልቅ ጀብዱ ድል እንዲመለሱ ለፋኖ አባለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘማች የፋኖ አባላት በበኩላቸው የኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነውን ህወሓት ከአማራ ክልል ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ዳግም የኢትዮጵያ ዜጎች ስጋት እንዳይሆን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሁሉም ዜጎች የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ወደ ክተት ጥሪ እንዲቀላቀሉና አካባቢውን በንቃት እንዲጠበቅ ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዊ ዞን ከሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።