የጄኔቫው ልዩ ስብሰባ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቀቀ

ታኅሣሥ 8/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ የጠራው የጄኔቫው ልዩ ስብሰባ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል፡፡
መድረኩ በመጀመሪያ ምዕራፍ ቆይታው የአባል አገራቱ እና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አባል አገራቱ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት ለእያንዳንዳቸው ሁለት ደቂቃ ተኩል እንዲሁም ለታዛቢ አገራት ደግሞ የአንድ ደቂቃ ተኩል ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
በስዊዘርላንድ በሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ አምስት ደቂቃ ተሰጥቷቸው አጠቃላይ ጉዳዮችን አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ የናቀና ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ለማስፈፀም ያሴረ መሆኑን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽሟል በሚል ሊነጋገርበት ቀጠሮ የያዘለት የውሳኔ ሃሳብ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው በጄኔቫ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የፊሊፒንስ ቋሚ መልዕክተኛ ኤቫን ጋርሽያ ገልጸዋል።
ስብሰባው ከሰዓታት ቆይታ በኋላ መካሄዱን ይቀጥላል፡፡