የጅቡቲ ስምምነት ትግበራ ላይ ያተኮረው 3ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክክር እየተካሄደ ነው

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) “ጥራት ያለው፣ አካታችና ተደራሽ ትምህርት ለስደተኞችና ከስደት ተመላሾች” በሚል ርዕስ ሦስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።
ምክክሩ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ዙሪያ እንዲሁም ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የፀደቀውን የጅቡቲ ስምምነት ትግበራ ላይ ያተኮረ ነው።
የምክክር መድረኩ በኢጋድ አባል አገራት ውስጥ ያለውን የትምህርት ተደራሽነት ችግርና ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ማግኘት ባለባቸው መሠረታዊ የትምህርት ዕድል ዙሪያ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሄው ላይ ትኩረት ያደረገ ስብሰባ ሲያካሂድ መቆየቱም ተመላክቷል።
እ.አ.አ መጋቢት ወር 2021 ከስምምነት የተደረሰበት የጅቡቲ ስምምነት የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰነዱ አባል አገራቱ ከራሳቸው የትምህርት ሥርዓት ጋር የተናበበ ጥራት ያለውና አካታች የትምህርት ሥርዓት እንዲዘረጉ የሚያስገድደው ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከአባል አገራትና ከተራድዖ ድርጅቶች ጋር ነው እየተመከረ የሚገኘው።
ውይይቱ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በማጠናቀቂያው ተጨባጭ ውሳኔዎች ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአስታርቃቸው ወልዴ