የጅቡቲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎታቸውን ገለጹ

የካቲት 7/2015 (ዋልታ) የጅቡቲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ፡፡

በጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሱፍ ሙሳ ዳዋሌህ የተመራ ልዑካን ቡድን የቂሊንጦ እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመጎብኘት የተከናወኑ የልማት ስራዎችንና የባለሀብቶችን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስራ እድል ፈጠራ፣ የኢንቨትመንት አማራጭ እና ለባለሀብቶች ስለሚደረጉ ማበረታቻዎች እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በተሰሩ ስራዎች ላይ ገለፃ ተደርጓል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ሽፈራው ሰለሞን ጉብኝቱ ከጅቡቲ በቅርብ ርቀት በተገነባው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የሀገሪቱ ባለሀብቶች ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሱፍ ሙሳ ዳዋሌህ በበኩላቸው የጅቡቲ ባለሀብቶች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ገብተው እንዲሰሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ መናገራቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡