የገበያ መረጃ ስርዓትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንዲመራ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ሚያዝያ 27/2014 (ዋልታ) የገበያ መረጃ ስርዓትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንዲመራ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሚኒስቴሩ ለአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች የተዘጋጀ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዳማ እያካሄደ ነው፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ሚኒስቴሩ ከተቋቋመት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ተቋማት ሲሰሩ የነበሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

ከነዚህም አንደኛው የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ማዕላትን አቅም በማጠናከር ጣቢያዎቹ ከክልሎች አንዲሁም ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር እንዲቀናጁ በማስቻል በሥራ ሀሳብ ፈጠራ የብድር አገልግሎት ማግኘት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲሠሩ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል፡፡

ሚኒስቴሩ ለዚህም የሚያግዝ የገበያ መረጃ ስርዓት በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንዲመራ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚኝ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ እንደ አገር 2ሺሕ 140 የሚሆኑ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፤ ይህንን የማስፋት ዕቅድም አለ ተብሏል፡፡

ከሰባት ክልሎች የተውጣጡ 2ሺሕ 260 የሚሆኑ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ አስተባባሪዎች በአገር አቀፍ የምክክር መድረኩ እየተሳተፉ ነው፡፡

በመድረኩ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ሰለሞን በየነ (ከአዳማ)