የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የስንዴና ዘይት ግዢ ተፈጸመ

ታኅሣሥ 26/2014 (ዋልታ) የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠርና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የ4 ሚሊየን ኩንታል ስንዴና የ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በጥቅምትና ኅዳር ወር የ4 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ግዢ መከናወኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ ከዚህም 1 ሚሊየን 51 ሺሕ 160 ኩንታል ስንዴ ወደ አገር ውስጥ ገብቷል፤ ይህም የስንዴ ዋጋ ከፍ እንዳይል አስተዋጽኦ ያደርጋል ብሏል፡፡
በተመሳሳይ የ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የምግብ ዘይትና ዱቄት ከውጭ አስመጪዎች በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገቡ በመደረጉ የሸቀጦች ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል ማስቻሉም ተገልጿል፡፡
በመሆኑም በጥቅምት ወር 34 ነጥብ 2 በመቶ የነበረ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በኅዳር ወር ወደ 33 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተነግሯል።
የኅዳር 2014 ወርሃዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ጥቅምት 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 8 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 1 ከመቶ የጨመረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡