የገቢ አሰባሰቡን በሚጎዳ ህገ-ወጥ ተግባር ተሰማርተው የነበሩ 63 ህገ-ወጥ ድርጅቶች ተያዙ

የገቢዎች ሚኒስቴር

ኅዳር 24/2014 (ዋልታ) የገቢዎች ሚኒስቴር ለአራት ወራት ባደረገው ምርመራ ከታክስ አስተዳደር ተሰውረው ሀሰተኛ ግብይት ሲያከናውኑ የነበሩና በህገ-ወጥ መንገድ የካሽ ሬጂስተር ማሽን ሲጠቀሙ የነበሩ 63 ድርጅቶች መያዛቸውን አስታወቀ።

በክትትል የተደረሰባቸው ህገ-ወጥ ድርጅቶች መከፈል የነበረበት ግብር እንዲሰወር በማድረግ በገቢ አሰባሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም ተገልጿል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሃያ ህገ-ወጥ የካሽ ሬጂስተር ማሽኖች ተይዘዋል፡፡

በህገ-ወጥ ተግባሩ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ይገኛልም ነው የተባለው፡፡

ሀገራቸውን የሚወዱ ከሰሩት ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ሳይሰስቱ በሚሰጡበት በዚህ ወቅት እንደዚህ ዓይነት ህገ-ወጥ ድርጅቶች ደግሞ ከእናት ሀገራቸው ይሰርቃሉ፡፡ ህዝባችን ከእናት ሀገራቸው የሚሰርቁ ድርጅቶችን ባለመታገስ ለሀገሩ በያገባኛል ስሜት መሳተፍ እንዳለበት ሚኒስቴሩ አሳስቧል።