የገናን በዓል በታሪካዊው ላሊበላ ለማክበር መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርግ ገለፀ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገናን) በታሪካዊው ላሊበላ ለማክበር እንዲቻል መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በላሊበላ ከተማ በመገኘት ታሪካዊውን የላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ በአብያተክርስቲያናት ላይ የደረሰ ጉዳት እንዳለ ጠይቀው በተሰጣቸው ምላሽ ለጊዜው የሚታይ ጉዳት ባይደርስበትም ጥናት እንደሚያስፈልገው ተነግሯቸዋል።
አሸባሪው ቡድን በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ስላደረሰው ግፍ፣ ዘረፋና ውድመት ከሃይማኖት አባቶች አንደበት አድምጠዋል።
አሸባሪው ቡድን በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ክፋቶችን ሁሉ መፈጸሙን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባበቢው ነዋሪዎችና ምዕመናኑ በቅርሱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ ላደረጉት ተጋድሎ አመስግነዋል።
ቀጣዩ ጊዜ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና የምታደርግበት መሆኑን ጠቁመው ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነት መከበር ክቡር ህይወታቸውን ጨምሮ ሁሉንም መስዋዕትነት ለከፈሉ እና እየከፈሉ ላሉ መላው የጸጥታ ኃይል አባላት ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ቀጣዩ የገና በዓል ሙሉ ክብሩን ጠብቆ በዚሁ ስፍራ እንዲከናወን መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።