የጉምሩክ ኮሚሽን ከወጪ ንግድ ከ112 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

ነሐሴ 03 ቀን 2013 (ዋልታ) – በተገባደደው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ112 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በ2013 የበጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጻሙንና ቀጣዩን ዕቅድ የሚገመግም መድረክ በሐዋሳ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንዳሉት፤ የተቋሙን አሰራር ማዘመን ተችሏል፡፡

ከወጪ ንግድ የሚመነጨውን ገቢ በሃላፊነት ለመሰብሰብ በተሰራው ሥራ በተገባደደው በጀት ዓመት ከ112 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ ቀደም ካለው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የሰባት ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።

በተቋሙ የአሰራር ሪፎርም መደረጉ፣ በቅንጅት መስራት፣ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ገቢውን እንዳሳደጉት ገልጸዋል።

ከወጪና ገቢ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ 38 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የተለያዩ ንብረቶችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለመንግስት ገቢ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።

የውስጥ አቅምን በአግባቡ አለመጠቀም፣ አጠቃላይ የንግድ ሥራ መቀዛቀዝና ቅንጅታዊ አሰራሩ ወጥ ያለመሆን በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።