የጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ 5230 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ማምረቱ ተጠቆመ

የጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) የጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኃይል የማመንጨት አፈፃፀሙ ከዕቅድ በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ሰሙ እንደገለፁት በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 4 ሺሕ 900 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለማመንጨት አቅዶ 5 ሺሕ 230 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በማምረት ከዕቅዱ በላይ የ4 በመቶ ብልጫ አስመዝግቧል፡፡

የኃይል ምርት አፈፃፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ19 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በመስከረም ወር የማመንጫ ዩኒቶችን ሊያስቆሙ የሚችሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ የመለዋወጫ ዕቃዎች መገዛታቸው ጣቢያው ከዕቅዱ በላይ ኃይል እንዲያመነጭ አስችሏልም ነው ያሉት፡፡

የጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ ንጉሴ ማሙሻ በበኩላቸው ለዩኒቶቹ ተከታታይነት ያላቸው የጥገና ሥራዎች በወቅቱ መከናወናቸው የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ከዕቅዱ በላይ ኃይል እንዲያመርት እገዛ አድርጓል ብለዋል፡፡

በዕቅድ ተይዘው እየተከናወኑ ካሉ የጥገና ሥራዎች ውጪ እስካሁን የማመንጫ ዩኒቶችን ሊያስቆም የሚችል ምንም ችግር እንዳልተከሰተም አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚያቅዳቸውን ዕቅዶች ከግብ እንዲያደርስ የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ግዢ ሊፋጠንና የስታፍ ፕላኑን የሚመጥን የሰው ኃይል እንዲሟላ ኃላፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከ40 እስከ 50 በመቶ እየሸፈነ የሚገኝና ኢኮኖሚውን በመደገፍ በኩል የጎላ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡