የጋማቤላ ክልል አመራሮችና ጋምቤላ ከተማ ማህበረሰብ ክፍሎች ውይይት በወቅታዊ ጉዳይ  

ነሐሴ 27/2013 (ዋልታ) ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ክልሉን ለማተራመስ የሚሹ የህወሃት ተላላኪዎችን አሳልፎ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቀረቡ።

የጋማቤላ ክልል አመራሮችና ከጋምቤላ ከተማ ከተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ውይይት አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ የህወሃት ተላላኪዎች በጋምቤላ ከተማ የፈጠሩት ሽብር በአኚዋክና ኑዌር የእርስ በእርስ ግጭት አድረገው ለማተራመስ ቢፈልጉም በመንግስትና በህዝብ ጥረት ከተማውን ማረጋጋት መቻሉን ተናግረዋል።

በድርጊቱ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ እጃቸው ያለባቸው ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ በየደረጃው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን በመወጣት ለመንግስት ጥቆማ በመስጠት የጋራ የሆነውን ሰላም መጠበቅ እንደሚቻልም አመልክተዋል።

ወጣቱ ሀገሩንና አከባቢውን በመጠበቅ ረገድ ሚናው ከፍተኛ እንደመሆኑ በማያውቀው እሳት ውስጥ እራሱን አሳልፎ መስጠት እንደሌለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ወላጆች በአከባቢያቸው የሚመለከቱትን አላስፈላጊ ድርጊቶች በአጭሩ መግታት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

ከተማዋን የሰላም ከተማ ለማድረግ ሁሉም የየድርሻቸውን ሊወጣ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደሩ አክለዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ታንኳይ ጆክ አሸባሪዎቹ ዋና ዓላማቸው ሁለቱ ቤሔረሰቦችን ግጭት ለመፍጠር መሆኑን አንስተው፣ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ህዝቡ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ህወሀት፣ ሸኔ እና ጋምቤላ ነፃነት ግንባር የተባሉት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ በጋራ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም በውይይቱ ተነስቷል።

በውይይቱ ላይም የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች መሳተፋቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።