የግብርና ዘርፍ ባለፉት 3 ዓመታት በዋና ዋና ተግባራት ከዕቅድ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡ ተገለጸ


መስከረም 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የግብርና ዘርፍ በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የመጀመሪያዎቹ 3 ዓመታት በዋና ዋና ተግባራት ከዕቅድ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከ2013 እስከ 2015 ዋና ዋና አፈጻጸሞች የግብርናው ዘርፍ ከዕቅድ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡን ሚኒስቴሩ ባወጣው ሪፖርት ያመላከተ ሲሆን በሪፖርቱ በ2013 ከነበረበት 5 ነጥብ 1 በመቶ በ2014 ወደ 5 ነጥብ 8 በመቶ እንዳደገና በ2015 ደግሞ 6̄ ነጥብ 3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ብሏል፡፡

ዘርፉ በስሩ ካሉት ንዑስ ዘርፎች መካከል ግብርናውን ለማሳደግ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የሰብል ምርት ሲሆን ለዘርፉ ማደግ 65.5 በመቶ አስተዋጽዖ ስያበረክት ደን 8.6 በመቶ እና እንስሳት 25.9 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸው ተመላክቷል፡፡

በ2015 ዓ.ም ጠቅላላ የሰብል ምርት 627 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 639 ሚሊየን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏልም ነው የተባለው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዘር የተሸፈነ መሬትን በተመለከተ የአነስተኛ አርሶ አደሮች በመኸር በአዝርዕት የተሸፈነ መሬት በ2012 ከነበረበት 13 ሚሊየን ሄክታር በ2015 ወደ 14.06 ሚሊየን ሄክታር ያደገ ሲሆን ይሄም በትላልቅ ኢንቨስትመንት በአዝርዕት ሰብል የተሸፈነ መሬት ብዙ ለውጥ ባለማምጣቱ ምክንያት ምርትና ምርታማነት ለጨመረው በዋናነት መሬትን ከማስፋት ይልቅ ምርታማነት ላይ ትኩረት በመደረጉ ነው ተብሏል።

በመስኖ የስንዴ ምርትን ከ2013 ከነበረበት 0.6 ሚሊየን ኩንታል በ2015 ወደ 47 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ እንደተቻለ እንዲሁም በግብርና ዘርፍ በእንስሳት ምርት አፈጻጸም ባለፉት 2 ዓመታት የእንስሳት ልማት ንዑስ ዘርፍ በአማካይ በ8.4% ያደገ ሲሆን ከ10 ዓመቱ ዕቅድ አንፃር በ0.8% ብልጫ አለው ተብሏል።

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በ2015 ዓ.ም 12.9 % ታቅዶ 10.8 % የቀረበ ሲሆን ለዚህም የፀጥታ ችግር እንደ አንድ መሰናክል በመሆኑ ከታቀደው በታች የሆነ አፈፃፀም ሊታይ ችሏልም ነው የተባለው፡፡

በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በከተማ ግብርናና በአትክልትና ፍራፍሬም ከፍተኛ ለዓለም ተሞክሮ የሚሆኑ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውንና ይህም በቀጣይ የመካከለኛ ዘመን ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን መገለጹን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡