የግብጽና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሚያሳዩት መወላወል የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጉዞ ወጥነት ያሳያል – ምሁራን

የግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሚያሳዩት መወላወል የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጉዞ ወጥነት እንደሚያሳይ ምሁራን ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ባስተላለፈችው ጥሪ መሰረት የግብጽ ልዑክ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች እና ታዛቢዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ቢገኙም ሱዳን ባለመገኘቷ የዕለቱ ስብሰባ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡

ያም ቢሆን አሁን አገራቱ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ተለዋዋጭ አቋም ማሳየታቸው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ትክክለኛ መንገድ ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው ሲሉ ዋልታ ያነጋገራቸው ምሁራን ተናግረዋል፡፡

በየመን የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሂ ቀድሞውኑ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር የተፋሰሱን ሀገራት ኢትዮጵያ በአንድ ማሰባሰብ በመቻሏ ግብፅ እና ሱዳን ደስተኞች እንዳልነበሩ ገልጸዋል፡፡

ከድርድሩ ጎን ለጎን ሁሉም የተፋሰስ ሀገራት በዓባይ አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ትዕግስት የተሞላበት ዲፕሎማሲ እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ሶስቱም ሀገራት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አስችሏል ብለዋል፡፡

ይህም ለኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ መጠቀም እንደሚገባት ህጋዊ እውቅና የሰጠ ከመሆኑም በላይ ለአባይ ግድብ መገንባት ድጋፍ የሚሰጥ አንቀፅ ተካቶበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሱዳን አቋም መለዋወጥ ሁለት ምክንያቶች እንዳሉት አቶ እንዳለ፣ ይህም ግብፅ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ የምታሳድረው ጫና እና በሱዳን ውስጥ ያለው የሽግግር መንግስት መንፈስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሙከረም ሚፍታህ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ በተለይም ከአሜሪካ ይደርስባት የነበረው ጫና አሁን ላይ መቀየሩን ተናግረዋል፡፡

በአሜሪካ በኦባማ ዘመን የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በትራምፕ ዘመን ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሙከረም፣ የትራምፕ አስተዳደር ቻይና በአፍሪካ ላይ ያላትን ተጽዕኖ ለመቀነስ በሀገራቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ስያሳድር እና በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ምሁራን ዘንድ መሳለቂያ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ይህ ሁኔታ በጆ ቫይደን የስልጣን ዘመን እንደሚቀየርም አንስተዋል፡፡

የሶስቱ ሀገራት ሚኒስትሮች የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ባለፈው ሳምንት የተወያዩ ሲሆን፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ባለሙያዎቹ የቀረጹትን ሰነድ በበጎ እንደሚመለከቱት እና በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆናቸውን መግለፃቸው ይታወቃል፡፡

(በደረሰ አማረ)