ሚያዝያ 25/2016 (አዲስ ዋልታ) በቅርቡ የሚመረቁት የጎርጎራ ፕሮጀክት እና የዓባይ ድልድይ ለሕዝብ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ዕድል እንደሚያስገኙ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ከአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ጋር በመሆን የዓባይ ወንዝ ድልድይን ጨምሮ የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እና የሌማት ቱሩፋት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በባሕር ዳር ከተማ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች ከአካባቢው ሕዝብ በተጨማሪ ለሀገርም ትልቅ ጸጋ ናቸው።
የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እና ውብ የሆነው የዓባይ ድልድይ በቅርቡ እንደሚመረቁ ጠቁመው ለባሕር ዳር ሕዝብ ብሎም ለሀገር ትልቅ የቱሪዝም ቱሩፋት እንደሚያስገኙ ተናግረዋል።
ሕዝቡ ሰላም እና ልማት እንደሚፈልግ ገልጸው ተገንብተው ከተጠናቀቁ እና ገና ከሚጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ለመሆን የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እና ማጽናት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ችግሮች ቢከሰቱ እና ጥያቄዎች ቢኖሩ እንኳን በሰለጠነ አግባብ እየተወያዩ የመፍታት ባህልን ማዳበር እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከዳር አድርሶ ተጨማሪ እና የተሻሉ የልማት ሥራዎችን ለመጀመር ሰላም የማይተካ ሚና እንዳለው አስገንዝበው “ሰላም ለልማት ትልቅ ቅድመ ኹኔታ ነው፤ ልማትም ለሰላም መሠረት ነው” ሲሉ የሰላም እና የልማትን ተመጋጋቢነት ገልጸዋል።
መንግሥት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሰላም ጥሪም በተደጋጋሚ እያደረገ ነው፤ የሰላምን ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ አሁንም ቃል እየመረጡ በመወርወር ሕዝብን ለማጋጨት መንቀሳቀስ እንደ ግለሰብ አክሳሪ ነው፤ እንደ ማኅበረሰብም ይጎዳል ነው ያሉት።
መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በመወጣት የኅብረተሰቡን ሰላም እንደሚያስጠብቅም ገልጸዋል።
የሰላም ጥሪው በግጭቱ ለተሳተፉ አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በሰላም ለመኖር አማራጭ የሌለው ምርጫ እና ትልቅ እድል ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ግጭት የገንዘብ ምንጫቸው የኾነ እና ያለግጭት መኖር የማይችሉ አካላት የሚያደርጉትን የጥላቻ ቅስቀሳ ጆሮ በመንሳት ሰላምን መምረጥ እና ሙሉ ጊዜን በልማት ላይ ማዋል እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።