የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ለሕልዉና ዘመቻው ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ሰበሰበ

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ጀምበሩ ሞላ  ለህልውና ዘመቻው ከ20 ሚሊየን ብር በላይ እና በአይነት ደግሞ ከ200 ኩንታል በላይ ሰንቅ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በሕልውና ዘመቻው የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎችና የወረዳው ነዋሪዎች የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።

የወረዳው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ ሰውነት ገዳሙ፥ ለሕልዉና ዘመቻው ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ የዘማች ቤተሰቦችን በተለያዩ መንገዶች እየደገፉ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

በዚህ በኩል የሴቶች አደረጃጀት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፥ ከስንቅ ዝግጅት ባሻገር ግንባር ድረስ ሂዶ ለመፋለም ሴቶች ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የወረዳው ነዋሪዎች ከሀብት ማሰባሰቡ በተጨማሪ ሰርጎ ገቦችን በመቆጣጠር እየሠሩ እንደሆነም ተገልጿል።

የወረዳው ነዋሪዎች ለሕልውና ዘመቻው እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን አሚኮ ዘግቧል።