የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ለአቅመ ደካማ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማእድ ማጋራት አካሄደ

ታኅሣሥ 29/2014 (ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናትና ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን የማእድ ማጋራት መርኃ ግብር አካሂዷል፡፡

ከ300 በላይ ለሚሆኑ አረጋውያን፣ አርበኞች፣ አካል ጉዳተኞች እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት የማእድ ማጋራት መርኃ ግብሩን ያዘጋጁት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ነው፡፡

የማእድ ማጋራት መርኃ ግብሩን  የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የሚኒስቴሩ የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ተፈሪ ፍቅሬ በጋራ በመሆን አስጀምረዋል፡፡

በዓሉን በማስመለከት ከአባትና ከእናት አርበኞች ተወካዮች የምስጋናና የምርቃት ስነ-ስርዓትም መካሄዱን ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡