የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራው ከፍተኛ ልዑክ የኢትዮጵያ የቡና ማሠልጠኛ ማዕከልን ጎበኘ

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) በጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያና ሴሬቲ የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ የቡና ማሠልጠኛ ማዕከል ጎበኘ፡፡

በጉብኝት መርሃግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት የተገኙ እንግዶች ተሳትፈዋል።

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ግቢ ውስጥ የተገነባው የቡናውን ዘርፍ አንድ እርምጃ ወደፊት ያስኬዳል ተብሎ የታመነበት ማሠልጠኛ ማዕከል በጣሊያን መንግስት እና በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ድጋፍ የተሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የማዕከሉ ግንባታ በጥምረት የምናካሂደውን የልማት ትብብር ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ማዕከሉ በምስራቅ አፍሪካ በዘርፉ የመጀመሪያው ዘመናዊ ማሠልጠኛ ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ ላይ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት በማሰልጠን እና በማብቃት የቡናውን ዘርፍ እንደሚያሻሽለው ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በቡና ምርምር ዘርፍ ላይ ከሚሠሩ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች እና የልማት አጋሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸውን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW