የጣና ፎረም ተጨማሪ የቱሪዝም እድል መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 9/2015 (ዋልታ) የጣና ፎረም ከውይይቱ ጎን ለጎን ተጨማሪ የቱሪዝም እድል በመሆን ትልቅ አሻራን ጥሎ አልፏል ሲል የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ::

የቢሮው ኃላፊ ጣሂር መሐመድ እንዳስታወቁት፤ ሰሞኑን በደኅንነት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በባህርዳር ከተማ የተካሄደው 10ኛው የጣና ፎረም ከጉባዔነት ባሻገር በአካባቢው ያለውን የኮንፈረንስ ቱሪዝም በማሳደግ ላይ ትልቅ አሻራ ጥሎ አልፏል::

ከሀይማኖታዊና ታሪካዊ ሁነቶች ባሻገር ለኮንፈረንሶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ቱሪዝሙን ማሳደግ እንደሚቻል ተሞክሮ ተወስዶበታልም ብለዋል::

በስብሰባ ምክንያት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚኖር እንቅስቃሴ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳለውም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ፎረሙ እንደ ክልል ባህር ዳር ከተማ ላይ እንደመካሄዱ በርካታ እንግዶች መገኘታቸውን ገልጸው ከፎረሙ መካሄድ አስቀድሞ እንግዶች የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ የማመቻቸት ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እንደነበርም አስረድተዋል::

በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትንና የሚመለከታቸው አካላትን ጨምሮ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ፎረሙን ከሚያዘጋጀው ሴክሬቴሪያት ጋር የጸጥታ፣ የመስተንግዶና አቀባበል ሥራዎች ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በትብብር መሰራታቸውንም አንስተዋል::

ፎረሙ ከጀምረበት ጊዜ አንስቶ እንግዶችን በመቀበል የማስተናገድ ሥራው ውጤታማ እንደነበር በመጥቀስ፤ ከአውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ባለው የእንግዶች አቀባበል የሀገርን ባህል ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ትዕይንቶች እንደነበሩ ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው::

በተጨማሪም ባህልንና በአካባቢው የቱሪስት መስህብ የሆኑ ሥፍራዎችን የማስጎብኘት ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል::

በፎረሙ ማጠናቀቂያም የሀገራት መሪዎች ጭምር በቅርበት የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውንና በዚህም ደስተኞች እንደነበሩ ኃላፊው ጨምረው ገልጸው ይህም ተጨማሪ የቱሪዝም እድል በመሆን ትልቅ አሻራን ጥሎ አልፏል ነው ያሉት::