የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከእስራኤል ልዑክ ጋር ምክክር እየተካሄደ ነው

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ትሕነግ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከእስራኤል ከመጣ ልዑክ ጋር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተካሄደ ነው።

የእስራኤል ልዑክ በእስራኤል የምክር ቤት አባልና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሆነው ጋዲ ባርካን የተመራ ሲሆን ልዑኩ የእስራኤል የምክር ቤት አባላትና የህክምና ባለሙያዎችን ያቀፈ ነው ተብሏል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) እስራኤልና ኢትዮጵያ የቀደመ የታሪክ ትስስር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተው የሀገራቱን ግንኙነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ የዚህ አንዱ ማሳያም የቤተ-እስራኤላዊያን ትስስር ነው ብለዋል።

አሸባሪው ትሕነግ በከፈተው ጦርነት በአማራና አፋር ክልል ከ1 ሺሕ በላይ ጤና ተቋማትን እንዳወደመም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከእስራኤል ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የእስራኤል ምክር ቤት አባል ጋዲ ባርካን በበኩላቸው ቤተ-እስራኤላዊያን ሁሌም ሌላኛዋ ሀገራቸው ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ዘርፈ ብዙ ቁርኝት እንዳላቸው ገልጸው የደረሰውን ውድመት በመመልከት የተቻላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ከእሰራኤል ልዑክ ጋር የመጡ እስራኤላዊያን በበኩላቸው ልዑኩ በዋናነት ያለውን ችግር በመለየት ለመደገፍ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በመድረኩ በአማራ ክልል ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ የዞን የጤና መምሪያ ኃላፊዎችና የወደሙ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጆች ተገኝተዋል፡፡

መስከረም ቸርነት (ከጎንደር)