የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከሶማሊያ አቻቸው ጋር ተወያዩ

ነሀሴ 17/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መከላከያ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከሶማሊያ አቻቸው ጋር በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ፡፡

የሶማሊያ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል አዲዋ የሱፍ ራጌ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያው አቻቸው ጀነራል ብርሀኑ ጁላ ጋር በተወያዩበት ወቅት  ሶማሊያ ወደፊት በወታደራዊ መስክ እራሷን ችላ ለመቆም በምታደርገው ጥረት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በሶማሊያ ውስጥ የሚገኘው አሸባሪ ቡድን አልሸባብ በሶማሊያ ህዝብ ላይ የሚያደረሰውን ጫና በመቀነስ ረገድ በአሚሶም ጥላ ስር ለግዳጅ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰራዊት የማይተካ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡

ጀነራሉ አክለውም የሶማሊያን ሰላም ለማስጠበቅ ቃል እየገቡ ከሚሄዱት የውጭ ሀገራት ይልቅ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጎረቤት ሀገሮች የሰሩት ተግባር ፅኑ ወዳጅነት በቃላት የሚነገር ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚረጋገጥ መሆኑ ማሳያ መስታወት ነው ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያው የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ  ሶማሊያ ራሷን ለመቻል በምታደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ ትብብር እና አጋርነት እንደማይለያት ቃል ገብተዋል፡፡

የጎረቤት ሀገር ሰላም የእኛም ሰላም ፤ የጎረቤት ሀገር ሰላም መናጋት የእኛም ስጋት በመሆኑ የጋራ ጠላታችንን እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ ዝግጁ ነን ማለታቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በመከላከያ ውጭ ግንኙነት የሁለትዮሽ ትብብር ጉዳዮች ዳይሬክተር ኮ/ል የኑስ ሙሉ ተናግረዋል፡፡