የፀረ ማጥቃት ዘመቻው መቀጠሉ ቀጥሏል – የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት

ጥቅምት 20/2014 (ዋልታ) – በአገር መከላከያ ሰራዊት እየተመራ ወራሪውን የሽብር ቡድንና ያሰለፈውን መንጋ እየመከተ የሚገኘው መላው የፀጥታ ኃይላችን በፀረ ማጥቃት እርምጃው ቀጥሏል ሲል መንግሥት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በተለይ ደሴን ለመያዝ አሰፍስፎ የመጣውን ወራሪ ኃይል በመመከት አኩሪ ገድልን እየፈፀመ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመላቷል፡፡

መግለጫው ሌሊቱን ሙሉ ከተለያዩ ግንባሮች ጠጋግኖ በማሰባሰብ ደሴን ለመያዝ በኩታበር፣ ቦሩ ሥላሴና በሃይቅ መስመር የመጣውን ወራሪ መንጋ የፀጥታ ኃይላችን በታላቅ ጀብዱ መክቶታል፤ አሁንም ደሴና አካባቢዋ በፀጥታ ኃይላችን ስር ነው ብሏል።

ቀደም ብለውም ስደተኛ በመምሰልና የመከላከያ ኃይላችንን ወታደራዊ አልባሳት ለብሰው ሊዘርፉ የሞከሩና ቡድኖችና በከተማዋ የሚኖሩ ለጥፋት ኃይሉ የሚሰሩ ባንዳዎች ከትናንት ጀምሮ የአሸባሪውን ዓላማ ለማስፈፀም ከግንባር ውጊያው ባልተናነሰ ሲሰሩ ውለዋል ሲልም አስረድቷል።

የደሴ ወጣቶችና መላው የፀጥታ ኃላችንም ይህንን ኃይል በተደራጀ መንገድ እየመከቱት ይገኛሉ። የከተማዋ ወጣቶችም በጀመሩት መንገድ ከተማቸውን ከባንዳ የመጠበቅ ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያለው።

ያለውን ኃይል ሁሉ አሰባስቦ በዚሁ ግንባር ያመጣው የሽብር ቡድኑ በጦር ግንባር ያቃተውን በወሬ ለማግኘት አሁንም መፍጨርጨሩን ቀጥሏል ሲል መንግሥት አሳውቋል።

አንዳንድ የውጪ መገናኛ ብዙኃንም የሽብር ቡድኑን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እያስተጋቡ ይገኛሉ።

በወሬ የሚያዝ ከተማ የለም ሊኖርም አይችልም ብሎ መላው ሕዝብ በደሴ ከተማ ዙሪያ ለሚነሳው አሉባልታ ጆሮ ሳይሰጥ አሁንም የአገሩን ኅልውና ለማስከበር የሚያደርገውን ተጋድሎ ቀጥሏል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለይ ያልተጣራ መረጃን በመያዝ ሕዝብን ለማሸበር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙና የሽብር ቡድኑ መጠቀሚያ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት በመግጫው አሳስቧል።