የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ ይወሰዳል

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቀ፡፡

የፌዴራል እና የክልሎች የፋይናንስ አስተዳደር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ሲሆን የምክክር መድረኩን የከፈቱት በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ዳይሬክተር ዳዊት ሽመልስ በሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና በክልል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንዲደረግ በገንዘብ ሚኒስቴር የወጣውን የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር በሀገሪቱ ዘመናዊ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ከወረዳ ደረጃ ጀምሮ ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመልካም አስተዳደር መጎልበት እንደ አንድ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

መመሪያው ተግባራዊ መደረጉ የዜጎች የመሰረታዊ አገልግሎቶች ቅድመ ፍላጎት በወረዳ ዕቅድ እንዲካተት በማድረግ፣ በበጀት አመዳደብና በወጪ አስተዳደር ተሳትፎ፣ በመሰረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ግምገማ፣ በመንግሥት ግዥ አፈፃፀምና የኦዲት ግኝት መረጃዎችን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያ ቁጥር 51/2010 ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመመሪያው ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት፣ በዘርፉ የሰለጠኑ በባለሙያዎች ከሥራ መልቀቅና መቀያየር ምክንያት ጉድለቶች ከመታየቸውም በላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ግጭትና አለመረጋጋት፣ የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን በቁርጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ ያላስቻሉ ችግሮች እንደነበሩ በመድረኩ ላይ መነሳቱን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!