የፌደራል ፖሊስ አባላት ከአሸባሪው ቡድን በተማረኩ ከባድ መሳሪያዎች የጠላትን ኃይል እየደመሰሱ መሆኑ ተገለፀ

ኅዳር 22/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ሀገርን ካላፈረስኩ በሚል የባንዳነት ተግባር ላይ ከተሰማራው የሕወሓት ጁንታ ቡድን በማረኩት ከባባድ መሳሪያዎች መልሰው ጠላትን እየደመሰሱ መሆኑን ኮማንደር ክንፈ ፀጋዬ ገልፀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት በጥምረት ሀገርን ለማፍረስ የተሰማራውን አፍራሽ ኃይል ከጀግናው የሀገር መከለላከያ ሰራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመሆን ጥቃት በመፈፀም በጠላት ኃይል ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እያደረሱ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡
አባላቱ በተሰማሩባቸው ግዳጆች ዲሽቃዎች፣ ብሬኖች፣ ቦንቦች፣ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች እና በርካታ ተተኳሽ ጥይቶችን እንደማረኩ የገለፁት ኮማንደሩ መሳሪያዎቹን እንደገና ለግዳጅ በማዘጋጀት በሰሜን ሸዋ ግንባር የጠላትን አከርካሪ እየመቱበትና እየደመሰሱ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡