የፌደራል ፖሊስና ኢትዮ ቴሌኮም በአማራ ክልል የወደሙ ተቋማትን ለማቋቋም የሚውሉ ቁሳቁስን ድጋፍ አደረጉ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና ኢትዮ-ቴሌኮም በአማራ ክልል በአሸባሪው ሕወሓት የወደሙ 178 ፖሊስ ጣቢያዎችን እና አምስት የዞን ፖሊስ መምሪያዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ10 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ለቢሮ ግብዓት የሚውሉ ቁሳቁስን ድጋፍ አደረጉ።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)  እና የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ መገኘታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ፖሊስ ጣቢያዎቻችንን ለሰላማችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላላቸው የወደሙትን መልሰን በመገንባት እና የፀጥታ ሥራዎቻችን የበለጠ ማጠናከር አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም ወንበር፣ ኮምፒውተርና ፕሪንተር የመሳሰሉ ድጋፎችን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከድጋፍ ጎን ለጎን ነፃ በወጡ የአማራ ክልል አካባቢዎች የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመጠገን የስልክ አገልግሎት በፍጥነት እንዲጀመር እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል ንፁሃንን በመግደል እንዲሁም ንብረታቸውን በመዝረፍና በማውደም አሰቃቂ በደሎችን መፈፀሙን ተናግረዋል።

ፖሊስ አሸባሪ ቡድኑ የፈፀመውን ግፍ በመመርመር ለፍትህ አደባባይ እንዲያቀርብልን እንፈልጋለን ሲሉም ጠይቀዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የመንግስት ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ አውድሟል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በክልሉ በ5 ዞኖች ብቻ 83 የሚደርሱ የፖሊስ ጣቢያዎች በሽብር ቡድኑ መውደማቸውን ጠቁመው ተቋማቱ የወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም ላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል።