የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ እያከናወነ ነው

ሐምሌ 27/2013 (ዋልታ) – የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ለሚኖሩ የ15 አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እያከናወነ ነው።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንደ ሀገር የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ከሚካሄደው የቤት ግንባታ በተጨማሪ የቤት ቁሳቁሶች እንደሚያሟሉም ተገልጿል።
በዚህ የክረምት መርሐ ግብር የ24 የአቅመ ደካሞች ቤት ለማደስ የታቀደ ሲሆን የ15ቱ ቤቶች ግንባታ በዛሬው ዕለት የተጀመረ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ግንባታቸው በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚጀመር ተገልጿል።
ግንባታውን ያስጀመሩት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በየአመቱ የምናደርገው የቤት እድሳት የተለያዩ መስሪያ ቤቶችን እና ባለሀብቶችን በማሳተፍ ባህል ልናደርገው ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከአዲስ አበባ ውጪ በሞጣ ከተማ አዲስ ከተማ በተባለ ስፍራም የ8 አቅመ ደካሞች ቤት እያሳደሰ መሆኑን ገልፀዋል።
(በነጻነት ጸጋይ)