የፌዴራል ፖሊስ በመምሰል የአንድን ግለሰብ ቤት ለመዝረፍ የተደረገ ሙከራ መክሸፉ ተገለጸ

መስከረም 14/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ የፌዴራል ፖሊስ በመምሰል የአንድን ግለሰብ ቤት ለመዝረፍ የሞከሩ ግለሰቦች እኩይ ሴራ በፀጥታ ኃይሎችና በህዝባዊ ሰራዊቶች ክትትል መክሸፉ ተገለጸ።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ኃይሉ ሉሌ አራት የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱና 2 ሲቪሎች ሆነው በግለሰብ መኖሪያ ቤት ሀሰተኛ የፌዴራል ፖሊስ መታወቂያ በማሳየት በር እንዲከፈትላቸው ካደረጉ በኋላ ሰራተኛዋን አግተው ዝርፊያ ሊፈፅሙ ሲሉ በአካባቢው በነበሩ የፀጥታ ኃይሎችና ህዝባዊ ሰራዊቶች ሴራቸው እንዲከሽፍ ተደርጓል ብለዋል።
የፀጥታ ኃይሎች ቀድሞም በነበራቸው ጥርጥሬ ዘራፊዎቹን ሲከታተሏቸው እንደነበረ የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ዘራፊዎች ከውጭ ባስቀመጧቸው ግብር አበሮቻቸው ቀድሞ አዘጋጅተውት በነበረው ኮድ 3 ኦሮ በሆነ ተሽከርካሪ ያመለጡ ቢሆንም ክትትል እየተደረገባቸው ይገኛል ብለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ቢያመልጡም በአካባቢው የደህንነት ካሜራ ስለነበረ ጉዳዩን ፖሊስ ይዞት ክትትል እያደረገበት እንደሚገኝ ገልጸው ማህበረሰቡ ራሱን ከመሰል አጭበርባሪዎች ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።
ወንጀል ሰርቶ ከሕግ ሊያመልጥ የሚችል ስለሌለ ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንደሚቀርቡም መገለጹን የክፍለ ከተማው ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።