የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሎች ከድጎማ በጀትና ከጋራ ገቢዎች የሚያገኙት የገቢ ድርሻ እየጨመረ መምጣቱን ገለጸ

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

ሰኔ 25/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ክልሎች ከድጎማ በጀትና ከጋራ ገቢዎች የሚያገኙት የገቢ ድርሻ እየጨመረ መምጣቱን ገለጹ፡፡

አፈ ጉባዔው በክልሎች መካከል የሚታየው ዕድገት ያልተመጣጠነ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በአዳማ ከተማ በበይነ መንግሥታት የፊስካል ግንኙነቶች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

አፈ ጉባኤው በምክክር መድረኩ ባደረጉት ንግግር የፌዴራል ተቋማት ወደ ክልሎች የሚተላለፉ ውስን ዓላማ ያላቸው በጀቶች እና የፌዴራል መሠረተ ልማት ዝርጋታ በአሠራራቸውም ሆነ በስርጭታቸው ፍትሃዊነት ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳባቸው እንደቆየ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ግልፅ፣ አሳታፊና ተጠያቂነት ያለው አሠራር በመዘርጋት በሚሠሯቸው ሥራዎች ፍትሃዊነትንና ውጤታማነትን እንዲያረጋግጡ ብሎም ክትትልና ድጋፍ እንዲሠጡ አሳስበዋል፡፡

ኃላፊነት የተሠጣቸው ተቋማትም የተዘረጉት አሠራሮች በትክክል ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ማረጋገጥ ያስችላቸው ዘንድ ደንብ ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡

ከተለያዩ ሀገራት የተገኙትን ተሞክሮዎች መሠረት በማድረግ፣ በሀገራችን ፍትሃዊና ውጤታማ የበይነ መንግሥታት ፊስካል ግንኙነቶችን ለማሳለጥ የሚያግዝ ሙያዊ ነፃነትና ብቃት ያለው ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት እውን ለማድረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሀገሪቱ ግልጽ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ የፊስካል ሽግግር ሥርዓቶች እንዲዘረጉ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ምክር ቤቱ ለብቻው ውጤት ማምጣት ስለማይችል ሁለቱ ምክር ቤቶች በተቀናጀ መንገድ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በአጽንኦት መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡