የፍትሕ ሚኒስትሩ ለአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባላት ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጡ

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

ሰኔ 16/2014 (ዋልታ) የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በብራስልስ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ከተለያዩ የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት ሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ አባላት ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰብዓዊ መብት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ማሪያ አሬና፣ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኡርማስ ፔት እና የአውሮፓ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል ጃቪየር ናርት ጋር መክረዋል።

በውይይታቸውም በሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰቱት ግጭቶች እና በሀገሪቱ ስላለው ወቅታዊ ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም መንግሥት ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተገናኘ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የወሰዳቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ ለፓርላማ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፓርላማ አባላቱ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ወቅታዊ መረጃ መለዋወጥ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ መካከል በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲፈጠር በቅርበት ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውም መግለጻቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ሚኒስትሩ ከሣምንት በፊት ከካርሎስ ዞሪህኖ የአፍሪካ፣ የካሪቢያን እና የፓሲፊክ መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ ፓርላማ ምክር ቤት ሰብሳቢ ጋር መወያየታቸውም ተመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW