የፍትሕ ሚኒስትሩ አንዳንድ ኤምባሲዎች ሽብርና ፍርሃት ለመፍጠር ቢሞክሩም አዲስ አበባ ሰላም ናት አሉ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) “በአዲስ አበባ አንዳንድ ኤምባሲዎችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሽብርና ፍርሃት ለመፍጠር ቢሞክሩም ህይወት በተለመደው መልኩ ቀጥሏል” ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከፍራንስ 24 ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በግንባር ተገኝተው ሰራዊቱን በመምራት ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

አሸባሪው ሕወሓት እያደረሰው ያለውን የዜጎች መፈናቀል፣ የንጹሃን ግድያና የንብረት ዝርፊያና ውድመት ለማስቆም እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

“የከተማዋ ነዋሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ጥበቃ እያደረገ ነው” ብለዋል።

‘በአዲስ አበባ ከፍ ያለ ብጥብጥ ይፈጠራል’ በሚል የሚናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን ለማረጋጋጥ ባንኮች፣ ትምህርት ቤቶች ሱቆችና የገበያ ማዕከሎችን ሁኔታ ተዘዋውሮ መመልከት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በሕግ ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች ምርመራ ተደርጎባቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትሩ ጌዲዮን፤ ሰዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በተጠረጠሩበት ወንጀል እንጂ የሚሰሩበትን ተቋም ወይም ማንነታቸውን መሰረት አድርጎ አለመሆኑን አስረድተዋል።