ሐምሌ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለዓለም የምናስተዋወቅበት መድረክ ይሆናል ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ፡፡
የቱሪዝም ሚንስቴር በፓሪስ ኦሎምፒክ ለሚሳተፉ አትሌቶች የሽኝት መርሀ ግብር አድርጓል::
አርብ የሚጀመረውን የፓሪስ ኦሎምፒክ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን የዓለም ህዝብ በቴሌቪዥን መስኮት እንዲሁም ከ8 ሚልዮን በላይ ህዝብ በአካል በመገኘት እንደሚመለከተው ይጠበቃል::
በዚህ ትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና ያሉንን የቱሪዝም ሀብቶች ከመክፈቻው እለት ጀምሮ አትሌቶቻችን በሚሳተፉባቸው በሁሉም ውድድሮች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ አምባሳደር ናሲሴ ተናግረዋል::
ለዚህም የሚሆን የተለያዩ የህትመት ስራዎች እና አልባሳት በቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል::
አትሌቶቻችን በሚያደርጓቸው ውድድሮች ካሸነፉ በኋላ ለ1 ደቂቃ ያህል በስታዲየሙ ውስጥ የሚከፈት የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት የሚገልፅ ሙዚቃ እና ምስልም ይፋ ሆኗል::
አምባሳደር ናሲሴ አትሌቶች፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ሚኒስቴሩ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ለሚያደርጉት አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል::
በለዊ በለጠ