የፓትሪስ ሉሙምባ ጥርስ ከቤልጂየም ወደ ኮንጎ ሊመለስ ነው

ሰኔ 13/2014 (ዋልታ) ኮንጎ ከቤልጂየም ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የኮንጎ የነጻነት አባት ፓትሪስ ሉሙምባ ጥርስ ከቤልጂየም ወደ ኮንጎ ሊመለስ መሆኑ ተነገረ፡፡

በኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣን ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ የሚመራ የሉሙምባ ቤተሰብ እና የኮንጎ ባለስልጣናት የልዑካን ቡድን ለዚህ ዝግጅት ብራስልስ ውስጥ ይገኛል፡፡

ኮንጎ ከቤልጂየም ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሉሙምባ በ1961 ተገድለዋል።

ፓትሪስ ሉሙምባ አብረው ከነበሩት ሁለት ሚኒስትሮች ጋር በግልጽ በማይታወቅ ሁኔታ መገደላቸው እና አስከሬናቸውም መጥፋቱ በታሪክ ተሰንዷል፡፡

ይሁን እንጂ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ እነርሱም የኮንጎ ጀግኖች ናቸው የተባሉት ሚኒስትሮቹ እንዴት እንደተሰው እውነታው ግልጽ መሆን ሳይችል ቆይቷል፡፡

ከበርካታ ዓመታት በኋላ በቤልጂየም በተደረገ ምርመራ ሰውነቱ ተቆርጦ በአሲድ መሟሟቱ ተረጋገጠ፡፡

በዚህም የሉሙምባ ጥርስ በቤልጂየም ፖሊስ ተወስዶ የነበረ ሲሆን ጥርሱ ለኮንጎ እንዲሰጥ የቤልጂየም ፍርድ ቤት ወስኗል፡፡

ኮንጎ ከቤልጂየም ነፃነቷን እኤአ በ1960 ካገኘች በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሉሙምባ በ1961 በአማፂያን የተገደሉ ሲሆን የቤልጂየም መንግሥት በግድያው ላይ እጁ እንደነበረበት ገልፆ በ2002 በይፋ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል፡፡