የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ተጫዋቾች ለመከላከያ ሰራዊት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገቡ

የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ተጫዋቾች

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ ተጫዋቾች ለመከላከያ ሰራዊት 40 ሚሊዮን ብር በላይ  ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የሊጉ ተጫዋቾች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ቦርድ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የቦርድ ሰብሳቢ አለቃ ፈቃደ ማሞ በሐዋሳ ከ16ቱም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በሚደረግበት ሂደት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ የገንዘብ ድጋፉ ይደረጋል ተብሏል።

የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች ”እንኳን እግር ኳስ መጫወት በሰላም ወቶ መግባት የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው” በማለት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግ በዱር በገደሉ የህይወት መስዋትነትን እየከፈለ ላለው ለሀገር መከላከያ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡት ተጫዋቾች መካከል የውጭ ሀገር አፍሪካውያን ተጫዋቾችም ”ይህ እኛንም ይመለከታል” በማለት ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል።

የክለቦቹ አመራሮችም ይህ ድጋፍ በደጋፊ ማህበራትም በኩል ተጠናክሮ በደም ልገሳ ለማስቀጠል ቃል መግባታቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።